Thursday 25 April 2013

ኮሎኔል መንግሥቱ ና የሰሞኑ ተናፋሽ ወሬ


የዚምባብዌ መንግሥት ባለሥልጣናት ስለ መንግሥቱ ማረፍ ስለሚናፈሰው ወሬ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለሐራሬ የዶቼቬለ ወኪል አስታውቀዋል ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አርፈዋል ሲል የዜምባብዌ ቴሌቪዥን መዘገቡን የሚጠቁሙ ፅሁፎች በአንዳንድ ብሎጎችና በፌስ ቡክ ተሰራጭተዋል ። ይሁንና የዚምባብዌ መንግሥት ባለሥልጣናት ስለ መንግሥቱ ማረፍ ስለሚናፈሰው ወሬ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለሐራሬ የዶቼቬለ ወኪል አስታውቀዋል ። ዴቼቬለ ዚምባብዌ ደውሎ በስልክ ያነጋገራቸው የ ኮሎኔል መንግሥቱ ዘመድ ነኝ ያሉ ግለሠብም የቀድሞው መሬ ሞተዋል የተባለው ሃሰት ነው ሲሉ ተናግረዋል ። ከ1983 ዓም አንስቶ ዚምባብዊ የሚኖሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ማረፋቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች በብሎጎችና በፌስ ቡክ ከወጣ ጥቂት ሳምንታት ተቆጥረዋል ። ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ የመረጃቸው ምንጭ የሚሉትም የዜምባብዊ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያን ነው ። ይሁንና የዚምባብዌ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ስለተናፈሰው ወሬ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ነው ያስታወቀው ።
ሃራሪ ዚምባብዌ የሚገኘው የዶቼቬለ ወኪል ኮሉምቡስ ማቭሁንጋ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ስለጉዳዩ ጠይቆ ያገኘውን መልስ ነግሮናል ።

«ዛሬ ጠዋት ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰዎችን ለማግኘት ሞክሬ ነበር ። አንድም ነገር አላረጋገጡም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ስለሚናፈሰው ወሬ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የሆነ ነገር ካለም በይፋ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል ። »
የደርግ ባለሥልጣናት
ዶቼቬለ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መኖሪያ ቤት በመደውል ስለተናፈሰው ወሬ ምንነት ለማጣራት ባደረገው ሙከራ ያነጋገራቸው ግለሠብ ፣ መንግሥቱ ምንም የደረሰባቸው ነገር እንደሌና ጤነኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ይህንኑ መረጃ በድምፅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት ግለሠብ የሚወራው በሙሉም ውሸት ነው ብለዋል ። በደወልንበት ወቅት ኮሎኔል መንግሥቱ በቤት ውስጥ እንደሌሉና ሌላም ስለርሳቸው ሊነግረን የሚችል ሰው እንደሌለም ገልፀዋል ። ጋዜጠኛ ኮሎምቦስ እንደሚለው ግን ስለ መንግሥቱ የጤንነት ሁኔታ ትክክለኛውን መረጃ ማግኘቱ አዳጋች ነው ።
« ስለ መንግሥቱ ለመናገር አስቸጋሪ ነው ። በዚምባብዌ የሚገፉት ህይወት ሚስጥራዊ ነው ። ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሰዎች አንዱ ናቸው ። ስለዚህ ጤናቸውም ሆነ የኑሮአቸው ሁኔታ በሚስጥር የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ። ብዙዎች ስርሳቸውን ማግኘት አይችሉም ። በዚህ የተነሳም በሚናፈሰው ወሬ ውስጥ እውነት መኖሩን ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል ። »
ኮሎኔል መንግሥቱ ዚምባብዌ ውስጥ አሁን ምን እንደሚሰሩ በይፋ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩን የጠቀሰው ጋዜጠኛ ኮሎምቦስ ሆኖም ከአመታት በፊት ለዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ በአማካሪነት መስራታቸውን ተናግሯል ።
«በይፋ ምን እንደሚያደርጉ አይታወቅም ግን እንደሚገባን የዚምባብዌ መንግሥት አማካሪ በመሆን ሳይረዱ አልቀሩም ። እንዲያውም እጎአ በ 2005 የሮበርት ሙጋቤ ZANU PF ፓርቲ መንግግሥት በሐራሬና በሌሎች ከተሞች አንዳንድ ቤቶችን ለማፍረስ ሲሠማራ የዚህ ፕሮጀክት ጠንሳሽ ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ነበሩ ። ይህም የሆነው የተቃውሞ ወገን የድምፅ ድጋፍ እንዲቀነስበት ለማድረግ ነበር ። ከዚህ ሌላ ስለ እርሳቸው እምብዛም የምናውቀው ጉዳይ የለም ። የሚታወቅ ነገር ቢኖር በሐራሬ እንደሚኖሩና በምሥራቃዊው የአገሪቱ ደጋማ አውራጃ የእርሻ ቦታ ያላቸው መሆኑ ነው ። ይህም የዚምባብዌ መንግሥት ከመደባቸው ለም የእርሻ ቦታዎች አንዱ ነው ። »
ኮሎኔል መንግሥቱ በ17 አመታት የሥልጣን ዘመናቸው ፈፅመውታል በተባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል በሌሉበት ሞት ተበይኖቦቸዋል ። የዚምባብዌ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ቻንጋራይ ከ 2 አመት በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ ሥልጣን ከያዙ ኮሎኔል መንግሥቱ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረው ነበር ።
« ከ2 ዓመት በፊት የተቃዋሚው ወገን በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራውን MDC ን አነጋግሬ ነበር ። ሥልጣን ላይ ከመጡ እርሳቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ነበር የMDC ሰዎች የገለጡልኝ ። ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለፍርድ እንዲቀርቡ ሃራሬና የአዲስ አበባ ግንኙነትም እንዲሻሻል ነው የሚፈልጉት እርገጠኛ ነኝ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ለኢትዮጵያ ተይዘው እንደሚሰጡ አያጠራጥርም ።»
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ

No comments:

Post a Comment