Sunday 7 April 2013

ኢሳት ዜና:




ተፈናቃይ አርሶአደሮች የደረሰባቸውን ጉዳት በመዘርዝር ለመንግስት ባለስልጣናት አቀረቡ

መጋቢት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በትናንትናው እለት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ከአማራ ክልል የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ፍኖተሰላም ከተማ ላይ ሰፍረው የሚገኙትን ተፈናቃዮች ያነጋገሩ ሲሆን፣ ተፈናቃዮችም ልዩ ሀይል እየተባለc በሚጠራው ታታቂ ቡድን የደረሰባቸውን ግፍ ያለምንም ፍርሀት ማቅረባቸውን በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አንድ ተፈናቃይ ገልጠዋል።
በስብሰባው ላይ ከአማራ ክልል መገናኛ ብዙሀን የተውጣ  ጡ ጋዜጠኞች ቢገኙም፣ ስብሰባውን እንዳይቀርጹ መደረጉን አንድ በስፍራው አለው የኢሳት ወኪል ገልጿል። አካባቢው በፌደራል በፖሊስ የሚጠበቅ በመሆኑን ፎቶግራፍ ማንሳትም ሆነ ሰዎችን ማነጋገር እንዳልተቻለ መኪላችን ገልጿል።
ከ 3 ሺ በላይ ተፈናቃዮች በፍኖተ-ሰላም ከተማ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል። በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናት እስካሁን ድረስ ይፋ መግለቻ አልሰጡም።


ለ3ኛ ጊዜ ህትመቱ የተቋረጠበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ” ከእንግዲህ ከጫካ መለስ ባሉ መታገያ መንገዶች በመጠቀም መብታችን እናስከብራለን” አለ

መጋቢት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይህን የተናገረው ልእልና ጋዜጣ በመንግስት ጫና እንዳድታተም ከታገደች በሁዋላ ነው። ጋዜጠኛ ተመስገን ” የንግድ ሚኒስቴር በልእልና ጋዜጣ የቀድሞ ባለቤትና በአዲሱ ባለቤት መካከል ህገወጥ የሆነ የስም ዝውውር ተደርጓል በማለት የንግድ ፈቃዱ  ” እንዲሰረዝ መደረጉን ተነግሯል።
ፍትህ ጋዜጣ በህገወጥ መንገድ እንዳይታተም ከተደረገ በሁዋላ፣ ጋዜጠኛው አዲስ ታይምስ መጽሄትን ከሌላ አሳታሚ ላይ በመግዛት ለተወሰኑ ሳምንታት ሲያሳትም ቆይቷል። መጽሄቷ በተመሳሳይ መንገድ እንድትዘጋ ከተደረገ በሁዋላ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን እንደገና ልእልና ጋዜጣን ከሌላ አሳታሚ ላይ በመግዛት ስራውን ለመስራት ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጅ ከ100 ሺ ብር በላይ በሆነ ወጪ የገዛው ጋዜጣ  ከመንግስት በተላለፈው ጫና እንዳይታተም በድጋሜ ታግዶበታል
ተመስገን በራሱ ስም ፈቃድ አውጥቶ መስራት ከተከለከለ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ስለሚኖረው አማራጭ ሲጠየቅ፣ “ያለኝ አማራጭ ከሲቪክ ተቋማት ጋር በመተባበር ፣ ከጫካ ትግል በመለስ ያሉትን የሰላማዋ ትግል አማራጮች በመጠቀም ፣ አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠር መብታችንን እናስከብራለን” ብሎአል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ሰሞኑን በገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ከፍተኛ ወከባ ሲደርስበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።  ተመስገን፣ ከ106 ያላነሱ ክሶችም እንዳሉበት ይታወቃል።

በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የደረሰውን መፈናቀል በመቃወም ፊርማ እያሳበሰቡ ነው

መጋቢት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያውያኑ ዛሬ በጀመሩት የፊርማ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ በርካታ የጀርመን ዜጎች ፊርማቸውን አኑረዋል፡ ዝግጅቱን እያስተባበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሲቪክና ፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የተባለው ገለልተኛ ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በላይ ወንድአፍራሽ ለኢሳት እንደገለጡት፣ ዝግጅቱ ለሚቀጥለው አንድ ወር ይቀጥላል።
የተሰባሰበውን ፊርማም ለጀርመን ፓርላማ፣ ለጀርመን የተለያዩ መሰሪያ ቤቶች፣ ለአውሮፓ ህብረትና፣ ለተለያዩ የአውሮፓ አገራት፣ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ለሂውማን ራትስ ወች ይቀርባል።
ጀርመናውያን የእኛ መንግስት ይህን መንግስት የሚደግፍ ከሆነ እንቃወማለን በማለት  ፊራማቸውን ሲያስቀምጡ መዋላቸውን የገለጡት አቶ በላይ፣ “ኢትዮጵያኖች ተሰባስብን በጋራ መጣር ካችልን ለውጥ እናመጣለን” ብለዋል።
በተመሳሳይ ዜናም ” የመንግስትን ህገወጥ ድርጊት” በመቃወም በአሜሪካ ዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሰኞ ኤፕሪል 8. 2013 ከጣቱ 9 ሰአት ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ ታውቋል።
መንግስት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው የአማራ ተወላጆች አሁንም በከፍተና ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ አስተዳደር በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ተጨማሪ ሰዎችን ለማፈናቀል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው ጥቆማ ያመለክታል።
ዜናው በመላ አገሪቱ ከተሰራጨ በሁዋላ ህዝቡ እየተነጋገረበት መሆኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በፌስ ቡክ “ስም አጉድፈሀል” የተባለው ተማሪ በ5 ሺ ብር ዋስ ተፈታ

መጋቢት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ አመት ተማሪ የሆነው  ማንያዘዋል እሸቱ ለኢሳት እንደገለጠው ከአንድ ሳምንት እስር በሁዋላ፣ የአርባ ምንጭ ፍርድ ቤት “ስትፈለግ ትመጣለህ” በማለት በ5 ሺ ብር ዋስ ለቆታል። ወደ ፈተና ለመግባት ሲዘጋጅ ሶስት ፖሊሶች መጥተው የፍርድ ቤት ማዘዣ በማሳየት እንደወሰዱትና በአርባ ምንጭ እስር ቤት አንድ ሳምንት ማሳለፉን ተማሪ ማንያዘዋል ገልጿል።
ተማሪ ማንያዘዋል፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በሙስና መዘፈቁን እንዲሁም በአገሪቱ ያለው የመብት አፈና መጨመሩን የሚገልጽ ጽሁፍ በድረገጽ አውጥተሀል ተብሎ መያዙን ገልጿል ።
አቃቢ ህግ በቂ ማስረጃ አላገኘሁም በማለቱ እንደተለቀቀ የገለጠው ተማሪ ማንያዘዋል፣ ይሁን እንጅ 5 ሺ ብር በሁለት ሳምንት ውስጥ እከፍላለሁ ብሎ ቃል በመግባት በመፈታቱ፣ ይህን ገንዘብ ካልከፈለ ወደ እስር ቤት እንደሚመለስ ተናግሯል። የደሀ ልጅ በመሆኑ ገንዘብ መክፈል እንደማይችል የገለጠው ተማሪ ማንያዘዋል፣ ፍርድ ቤቱ ቶሎ ውሳኔ ቢሰጠው ከጭንቀት እንደሚገላገልም ገልጿል። “አሁን ከአሁን መጥተው ይወስዱኝ ይሆን” በማለት  ትምህርቱን ተረጋግቶ መማር እንዳልቻለም ተናግሯል።
በጠባብ ክፍል ውስጥ 25  ሰዎች ታስረው እንደነበር፣ ከሙቀቱ በተጨማሪ ቱሁዋን አስቸግሮት እንደነበር አልሸሸገም። ተማሪ ማንያዘዋል ፖሊሶች እና ፍርድ ቤቱ ላደረገለት ትብብርም ምስጋና አቅርቧል።
ተማሪ ማንያዘዋል 4 ነጥብ በማምጣት ዩኒቨርስቲ መግባቱም ታውቋል። በሚማርበት ዩኒቨርስቲም እንዲሁ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ አለ የ21 አመት ወጣት ነው።
ESAT

No comments:

Post a Comment