Monday 7 July 2014

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ሂውማን ራይትስ ወች ገለጸ

ሰኔ ፴(ሠላሳ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ፣ አቶ አንዳርጋቸው ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ተደርጎ ለኢህአዴግ የጸጥታ ሃይሎች ተላልፎ መሰጠቱን ከታማኝ ምንጭ ማግኘቱን ገልጿል።

የየመን ባለስልጣናት ሰነዓ ከሚገኘው ኤል ራህባ አየር ማረፍያ ላይ እኤአ ጁን 23 ወይም 24 ከእንግሊዝ ኢምባሲ ጋር እንዳይገናኝ አድርገው አቶ አንዳርጋቸውን ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ ልከውታል ሲል ሂውማር ራይተስ ወች አስታውቋል።
የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው የአቶ አንዳርጋቸው ደህንነት እንደሚያሰጋቸው ገልጸው፣ መንግስት ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጠበቆቻቸውና ከእንግሊዝ ኮንሱላር ሰራተኞች ጋር እንዲገናኙ እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።
አለም በሙሉ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በአንክሮ እየተከታተለው መሆኑን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ልብ ሊሉት ይገባል ሲሉ ሌፍኮው ተናግረዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን በሃይል ወደ ኢትዮጵያ እንዲወሰዱ መደረጋሸውን  በአገሪቱ የሚገኙ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ከፍተኛ የሆነ ስቃይ እንደሚደርስባቸው የገለጠው አምነስቲ፣ በአቶ አንዳርጋቸውም ላይ ከፍተኛ ስቃይ ሊደርስበት ይችላል ሲል አክሏል።
አምነስቲ አያይዞም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጎረቤት አገሮች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር በርካታ ኢትዮጵያውያን ያለፍላጎታቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ስቃይ እንዲደርስባቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
አምነስቲ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው የታሰረበትን ቦታ እንዲያስታውቁ ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment