Wednesday, 16 July 2014

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ እርዳታ ፖሊሲ ተግባራዊነት እንዲፈተሽ ታዘዘ

የእንግሊዝ የባሕር ማዶ ትብብር ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሲሰጥ ከራሱ የሰብዓዊ መብቶች ፖሊሲዎች ጋር በተጣጣመ መልክ መሆንና አለመሆኑ እንዲፈተሽ አንድ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት መወሰኑን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች አድንቋል፡፡

ዲፊድ፤ ሂዩማን ራይትስ ዋች እና መንደር ምሥረታ በኢትዮጵያ

የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት፤ ሐምሌ 7/2006 ዓ.ም ባሣለፈው ውሣኔ የዓለም አቀፍ ትብብር መሥሪያ ቤቱ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሲሰጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በበቂ ሁኔታ አይፈትሽም ሲባል የቀረበበት ክሥ ሙሉ የፍርድ ቤት ምርመራ የሚያስፈልገው ነው ብሏል፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ መርኃግብር ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ቃል ይህ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ውሣኔ ገና የመጀመሪያ እርምጃና ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
ሌስሊ ሌፍኮው - የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ መርኃግብር ምክትል ዳይሬክተር
ጋምቤላ
በጋምቤላ፣ በሶማሌ ክልልና በደቡብ ኦሞ እየተፈፀሙ ናቸው ያሏቸው አድራጎቶችም የቅርብ ፍተሻ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን የጠቆሙት ሚስ ሌፍኮው ልማት ከሰብዓዊ መብቶች መከበር ጋር አብሮ መታየት እንደሚገባቸው ለጋሾች ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል ሚስ ሌፍኮው፡፡
መሠረታዊ የልማት ድጋፍ ይቁም የሚል አቋም ሂዩማን ራይትስ ዋች እንደሌለው ሌፍኮው አመልክተው የእንግሊዝ መንግሥት ለኢትዮጵያ በሚሰጠው እርዳታ ሰብዓዊ መብቶችን የሚረግጡ ፕሮጀክቶችን የሚያስፈፅሙ ባለሥልጣናት ደመወዝ እንደሚከፈል አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ አስታያየት እንማይሰጥ የተናገረው የእንግሊዝ የዓለምአቀፍ ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የሠፈራ መርኃግብር የገንዘብ ድጋፍ ሰጥታ እንደማታውቅ ገልጿል፡፡
“መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመጠበቅ የምንሰጠው ድጋፍ የሚውለው እንደ ጤናጥበቃ፣ ትምህርት ቤቶች እና ንፁህ ውኃን ለመሳሰሉ አገልግሎቶች ነው” ብሏል መሥሪያ ቤቱ በኢሜል በሰጠን ምላሽ፡፡
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም የሠፈራ መርኃ ግብሩ የሚካሄደው በሠፋሪዎቹ ፍቃደኝነትና በግልፅነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሰዎች በቀልን በመፍራት ምክንያት አስተያየቶቻቸውን ለመግለፅ እንደማይፈልጉና መንግሥቱ በመገናኛ ብዙኃን ላይ በተከታታይ አፈና እየፈፀመ መሆኑን የሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጫ አመልክቷል፡፡
እንግሊዝ ለኢትዮጵያ በየዓመቱ የ300 ሚሊየን ፓውንድ እርዳታ እንደምትሰጥ ሂዩማን ራይትስ ዋች የጠቀሰ ሲሆን ሌፍኮው በሰጡት ቃል “የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ግን በተከታታይ እያሽቆለቆለ ነው” ብለዋል፡፡
"የእንግሊዝ የውጭ ተራድዖ መሥሪያ ቤት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ግድ የሚሰጠው ከሆነ በመንደር ምሥረታ መርኃግብርና በሌሎችም አሠራሮች የሚፈፀሙ ብርቱ የመብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም የሚያስችል ጫና ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ የክትትልና ግምገማ ሥርዓቱን መልሶ መፈተሽና ሙሉ በሙሉ ማስተካከል ይኖርበታል" ሲሉ ሌስሊ ሌፍኮው አሳስበዋል፡፡
http://amharic.voanews.com/

No comments:

Post a Comment