Wednesday 2 October 2013

አባይ Vs ስብሃት ኔትዎርክ

-------------------------------

ዛሬም (እንደወትሮው) አንድ ቀሽም አስተያየት ልስጥ!

በህወሓት ዉስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ እያየን ነው። ስብሃት ነጋ የሚዘውረው ቡድን አንሰራርቶ የፖለቲካ የበላይነቱ የሚቆጣጠርበት ዕድል ሊኖር ይችላል (መላምት ነው፣ ከውዲሁ በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም)። የስብሃት ነጋ ኔትዎርክ ህወሓት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ የትግራይ ህዝብ ጠፍሮ ሲገዛና ሲያሰቃይ የነበረ ነው።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በሆነ ዉስጣዊ አለመግባብት ምክንያት የስብሃት ኔትዎርክ እየተመናመነ መጣ። አቶ አባይ ወልዱ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት ከሆነ በኋላ ኔትዎርኩ በሌሎች ተተካ። ይባስ ብሎ ደግሞ ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ አቶ አባይ ወልዱ የህወሓት ሊቀመንበር ሆነ። ከዚህ ግዜ ወዲህ ስለ አባይ ወልዱ ባህሪ መጥፎነትና የፖለቲካ ብቃት ማነስ በሰፊው ይወራ ጀመር።

እኔ የሌሎች የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያህል የአባይ ወልዱ የተሟላ መረጃ የለኝም። እንደሌሎቹም በሓሳብ ክርክር ፊት ለፊት ተገናኝተን አናውቅም። (መለስ፣ ስብሃት፣ ስዩም፣ አባይ ጸሃየ፣ አርከበ፣ ቴድሮስ ሓጎስ፣ ፀጋይ በርሀ ... ብዙዎቹ በደንብ አቃቸዋለሁ)። አባይ ወልዱ ግን በደንብ አላውቀውም። አንድ ግዜ ብቻ በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተን ብዙ አውርተን ነበር (አብርሃ ደስታ መሆኔን ሳያውቅ ማለት ነው)። ያኔ እንዳየሁት ትህተኛ (humble) ይመስላል (በአንድ ግዜ የሰው ባህሪ ለመገምገም ቢከብድም)።

ስለዚህ ስለ የአባይ ወልዱ ፖለቲካዊ ብቃትና የግል ባህሪ ጥሩነት ወይ መጥፎነት መመስከር አልችልም። ቁልፍ የሚባል የህወሓት ስልጣን ለባለቤቱ መስጠቱ ግን እንደማንኛውም ሰው ገርሞኛል። ይህ እንዳለ ሁኖ ስለ አባይ ወልዱ አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ። አባይ በህወሓት ካድሬዎች አይወደድም። አባይ የአምባገነንነት ባህሪ እንዳለውና የፖለቲካ ብቃት እንደሚያንሰው ለህዝቡ እንዲደርስ ተደርጓል። ማነው ስለ አባይ መጥፎነት የሚያወራ ቢባል መልሱ የህወሓት ካድሬዎች መሆናቸው ግልፅ ነው።

ለምን? አባይ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ከመሆኑ በፊት ቁልፍ የህወሓት ኔትዎርክ ተቆጣጥረው የነበሩ ካድሬዎች የስብሃት ነጋ ታማኞችና ዘመዶች ነበሩ። ትግራይ ሙሉ ተቆጣጥረውት ነበር። አባይ ወልዱ የነሱ ዘመድ አይደለም። አባይ ስልጣኑ ከጨበጠ በኋላ የስብሃት ታማኝ ኔትዎርከኞች ስጋት አደረባቸው። ስጋታቸውም የህወሓት ኔትዎርከኞች ቀስ በቀስ ይቀየራሉ፤ ቁልፍ የሆኑ የስልጣን እርከኞችም ከስብሃት ታማኞች ወደ አክሱም ተወላጆች ይሸጋገራሉ የሚል ነበር።



የስብሃት ህወሓቶች አንድ ሰው ከስልጣን ለማውረድ ወይም ስልጣን ለመስጠት ሲፈልጉ ስለሰውየው የፈጠራ ወሬ (የሚያዋርድ ወይ የሚያስወድስ) ለህዝብ ይነዛሉ። በቂ ኔትዎርክ ስላላቸው እነሱ የፈለጉትን ወሬ ከህዝብ ለማድረስ አይቸገሩም። እነሱ የፈልጉትን ሰው ወደ ስልጣን ለማውጣት ስለሰውየው ጥሩ ነገር ያወራሉ፤ ካልፈለጉት ደግሞ ስሙን ያጠፉታል። በዚህ መንገድ ስልጣን ወደ አክሱም ተወላጆች እንዳይሸጋገር በመስጋት የአባይን ስም ከማጥፋት አልቦዘኑም። አባይ ብቃት አለው ወይ የለውም ለሚለው ሰው ትክክለኛ ግንዛቤ የለውም።

በትክክልም አባይ የቀድሞው የኔትዎርከኞቹ ማንነት በተቻለ መጠን ቀይሮታል። እንደፈሩት አልቀረም። ነገር ግን የአባይ ኔትዎርክ እግር ሳይተክል ፈተና ገጥሞታል። የስብሃት ኔትዎርክ እንደገና የሚያንሰራራበት ዕድል እያገኘ ይመስላል። ለትግራይ ህዝብ (በኔ እምነት) ከስብሃት ኔትዎርክ የአባይ ኔትዎርክ በብዙ እጥፍ ይሻላል። ምክንያቱም የአባይ ኔትዎርክ ከሞላ ጎደል ለዘብተኛ ነው። የስብሃት ግን መርዘኛ ነው። ትግራይ በተወሰኑ የቤተሰብ አባላት ስር የወደቀችበት ምክንያት በስብሃት ኔትዎርክ ነው። (አሁን አባይም ተመሳሳይ ነገር የጀመረ ይመስላል)።

ምናልባት ስብሃት ከተሳካለትና ትግራይን መልሶ ከተቆጣጠረ አደገኛ ስለሚሆን የሽግግሩ ግዜና አጋጣሚ ተጠቅሞ ዓረና ፓርቲ የህወሓት አመራር አባላት በማሳመን በህወሓት ዉስጥ ህቡእ የዓረና አባላት የሚፈሩበት መንገድ መመቻቸት አለበት። ህወሓትን ማሸነፍ የምንችለው ወደ ህወሓት ዘልቆ በመግባት ነው። ህወሓት ዉስጡ ስለበሰበሰ ፓርቲው ዉስጥ ገብቶ ኔትዎርኩን መቆጣጠር ያን ያህል የሚከብድ አይሆንም።

It is so!!!

Abraha Desta

No comments:

Post a Comment