Thursday 27 June 2013

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቀልን አሉ


ቀድሞ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ ነዋሪ የነበሩና በኋላ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገብተው በቤሌ ጃጐንፎይ ወረዳ የተዛወሩ 44 አባወራዎች፣ ‹‹በመንደር ማሰባሰብ›› ስም በ2003 ዓ.ም. የክልሉ መንግሥት እንዳፈናቀላቸው በተወካዮቻቸው አማካይነት አስታወቁ፡፡ 
ተፈናቃዮቹ እንደገለጹት፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር አዋሳኝ በነበረውና በ2000 ዓ.ም. ወደ ክልሉ በተቀላቀለው ይዞታቸው ላይ ለሃያ አምስት ዓመታት ኖረዋል፡፡ በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ሰብስቦ ካወያያቸው በኋላ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መቀላቀላቸውን እንዳሳወቃቸውና ጉዳዩ የመንግሥት ውሳኔን የተከተለ በመሆኑ፣ ነዋሪዎቹ ወደ ቤኒሻንጉል ክልል መቀላቀላቸውን ይናገራሉ፡፡ ከነዋሪዎቹ ጋር የተደረገው ውይይትም ሰላማዊ መሆኑን፣ ነገር ግን ወደ ቤኒሻንጉል ክልል እንዲካለሉ ከመደረጉ በፊት ድንበርተኛ እንደመሆናቸው ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ 
ምንም እንኳ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሲከለሉ አካሄዱ በውይይትና በማሳመን የነበረ ቢሆንም፣ ለመንደር ማሰባሰብ በሚል የክልሉ መንግሥት በ2003 ዓ.ም. ፈጽሞ ሳያሳውቃቸው ግብር ከሚገብሩበት መሬታቸው ላይ ማስነሳት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ከተፈናቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ለቀበሌ፣ ለወረዳ፣ ለዞንና ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ዛሬም አቤቱታቸው ሰሚ ጆሮ አላገኘም ይላሉ፡፡ ለረዥም ወራት ቤትና መሬት አልባ ሆነው የነበራቸውን ሀብትና ንብረት ሸጠው በመጨረስ የዕለት ጉርስ እስከመቸገር መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡ 
‹‹በ2003 ዓ.ም. ሳናርስ ቀረን፤ ነገሮች ይለወጣሉ ብለን ብናስብም በ2004 ዓ.ም. እንዲሁ ስንንከራተት ጊዜው አለቀ፤›› የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ ለተፈናቀሉት አባወራዎች ተለዋጭ መሬት እንዲሰጣቸው ቀነ ገደብ ቢያዝም፣ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱን አስረድተዋል፡፡ 

በሐምሌ 2004 ዓ.ም. ጉዳዩን በሚመለከት ውይይት ያደረጉት የሚመለከታቸው የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የመንግሥት ኃላፊዎች፣ አሥራ ሰባት ተፈናቃይ አባወራዎችን በመንደር ለማሰባሰብ ተነስተው፣ ቤትና ትምህርት ቤት ሳይሠራበት የቀረ መሬት ላይ እያረሱ እንዲቆዩ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር ብለዋል፡፡ በየካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ መሬት እንዲያገኙ መወሰኑን የሚያሳይ ቃለ ጉባዔ ቢኖርም፣ ውሳኔው ዛሬም ድረስ ተግባራዊ መሆን አልቻለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 
በተመሳሳይ ባለፈው ወር ማብቂያ ላይ የተፈናቃዮቹ ጉዳይ የሚመለከታቸው ክልሎችና የመንግሥት ኃላፊዎች ጥምር ኮሚቴ ውይይት አካሂዶ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ለተፈናቃዮቹ ተለዋጭ መሬት የመስጠቱ ሒደት እስከ ሰኔ 5 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ በቃለ ጉባዔ ውሳኔ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ውሳኔው ተፈጻሚ ሊሆን አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም ባለፈው ሳምንት እንደገና አቤቱታቸውን ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡ 
የተፈናቃዮቹ ጉዳይ በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተያዘ መሆኑን ማረጋገጥ ያልተቻለ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው ኃላፊ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ማግኘት አልተቻለም፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስርን በስልክ ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተው ነገር ግን ለምን ተፈጻሚ እንዳልሆነ አለማወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ማን ዘንድ እንዳለ እንደሚያዩት አቶ አህመድ አስረድተው፣ ለጊዜው ከዚህ በላይ በዝርዝር ለማብራራት እንደማይችሉ አስታውቀዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment