Thursday 7 November 2013

የህወሓት ተግባር የተቃወሙ የፖልዮ ክትባት እንዳያገኙ ተደረገ!


በትግራይ ክልል እንደርታ ወረዳ ነው። ልዩ ስሙ “እግሪ ሓሪባ” (ኲሓ አከባቢ መሆኑ ነው) ይባላል። ኗሪዎቹ በከተማነት ጉዳይ ከአከባቢው አስተዳደር አልተግባቡም። እስከ ክልል መጥተው ጥያቂያቸው አቅርበዋል። መፍትሔ አላገኙም። ተስፋ ሳይቆርጡ ተቃውሞአቸው ቀጠሉ።
በህዝቡ የከረረ ተቃውሞ ያኮረፈ የሕወሓት መንግስት ኗሪዎቹ ምንም ዓይነት የመንግስት አገልግሎት እንዳያገኙ ወሰነ (ለህወሓት ካልታዘዙ ማለት ነው)። በዚህ መሰረት ኗሪዎቹ ለሁለት ዓመት ያህል ምንም የመንግስት አገልግሎት አላገኙም (እስካሁን ድረስ አያገኙም)። የፖሊስና ፀጥታ አገልግሎት የለም፣ የፍርድቤት አገልግሎት የለም (የግድያ ወንጀል የፈፀመም በሕግ አይጠየቅም፣ ምክንያቱም ፍርድቤት የለም)፣ ትምህርትቤት የለም ….. ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች የሉም።

የኗሪዎቹ ልጆች ለሁለት ዓመት ያህል ትምህርታቸው አቋርጠዋል። በህወሓት ዉሳኔ ያዘኑ ወላጆች በ2006 ዓም የትምህርት ዘመን ልጆቻቸው በከተማ ትምህርትቤት ለማስተማር ወሰኑና አስመዘገቡኣቸው። የህወሓት ካድሬዎችም የህፃናቱ ማንነት እያጣሩ ከትምህርትቤቱ አባረሩዋቸው። ግፍ ነው።
በቅርቡ ደግሞ መንግስት ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት የፖልዮ ክትባት እንደሚሰጥ ማቀዱ ሰምተናል። የእግሪ ሓሪባ ህፃናት ግን የፖልዮ ክትባት እንዳያገኙ ተከለከሉ። በህይወት (በጤንነት) የመኖር መብታቸውም ተነፈጉ።
ለነዚህ ህፃናት አቤት የሚል የለም። ምክንያቱም ከእንደርታ ወረዳ የተወለደ ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣን የለም። የድሮ ታጋዮችም ቢሆኑ አሁን እዚሁ መናገር በማንችለው ምክንያት ህይወታቸው ጠፍቷል (ወይ እንዲጠፉ ተደርጓል)።
አሁን በእግሪ ሓሪባ ተዘግቶ ያለ ትምህርትቤት “ወዲ ዓይነታ ትምህርትቤት” ይባላል። ወዲ ዓይነታ (ተከስተ ሃይሉ) የድሮ የህወሓት ታጋይ የሆነ የአከባቢው ተወላጅ ነው። ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ህይወቱ እንዲያልፍ ተደርጓል።
ሌሎች የእንደርታ ተወላጆች በድሮ የህወሓት ትግል ቁልፍ ሚና የነበራቸውና የህወሓት መሪነት ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ጥያቄ በማንሳታቸው “በአዋራጃዊነት” ተፈርጀው በ’ሕንፍሽፍሽ’ ስም ዒላማ ተደርገው የጠፉ እነ ተስፋማርያም ሕሸ፣ ታደሰ ዕንጭቂት፣ ኪሮስ ገሰሰ ወዘተ ነበሩ። አሁን ማንም የቀረ የለም።
ወዲ ዓይነታ ትምህርትቤትም ተዘግቷል። አሁን ማን ይከፍተዋል? አሁን ማን ልጆቹን የፖልዮ ክትባት እንዲያገኙ ይማጎታል? ማንም የለም?
እስቲ ለሁላችን በእኩል የሚያገለግል ስርዓት ለመገንባት እንታገል።
Abraha Desta

No comments:

Post a Comment