ኢህአዴግ የዞን9 ጦማሪዎችን “አገር በማተራመስ” ወንጀል ከሰሰ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የኢትዮጵያ ጉዞ በርካታ ጉዳዮች የሚከናወኑበት እንደሆነ ተጠቆመ። የዘወትር የጎልጉል ምንጭ አንዳሉት የኬሪ አዲስ አበባ ጉዞ አስቀድመው የተሰሩ ስራዎች ውጤት ነው። ጥቁሩ ሰው “ውሻ ምንም ሳይመለከት አይጮህም” ሲሉ አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ብቃት ያላቸው አማራጮች መሆናቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል። ኢህአዴግ አሜሪካንንና የምዕራቡን ዓለም እንደለመደው “ከሶማሊያ ጦሬን አወጣለሁ” በማለት መደራደሪያ ከማቅረብ ውጪ ሌላ አቅም እንደሌለው ተገለጸ። ኢህአዴግ የዞን9 ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች “አገር በማተራመስ” ወንጀል ክስ መሰረተባቸው።
የድረገጽና የማህበራዊ ገጽ የኢህአዴግ ደጋፊዎችና የስርዓቱ ተጠቃሚ አባላት ባይዋጥላቸውም አሜሪካና ኢህአዴግ የነበራቸው ግንኙነት እየሻከረ መሔዱን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል። ጎልጉል የዋሽንግቶን ዲፕሎማት ምንጩን በመጥቀስ እንደዘገበው አሜሪካ ኢህአዴግን “የምስራቅ አፍሪካ ስጋት” አድርጋም ፈርጃለች። የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተለውና በስቴት ዲፓርትመንት ውስጥ የተቋቋመው የቀውስ መከላከልና ዕርቅ ቢሮ ሃላፊ ከጥር ወር ወዲህ ባሉት ጥቂት ወራት ውስጥ አራት ጊዜ አዲስ አበባ ተጉዘዋል።
ኢህአዴግ እየተከተለ ያለው ፍትሃዊነት የጎደለው አገዛዝ ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ እንዳመራትና ይኸው ቀውስ እልባት ካልተበጀለት የምስራቅ አፍሪካን የሚያዳርስ እንደሚሆን በአሜሪካ በኩል አቋም መያዙ ኢህአዴግን እንዳስበረገገው ተንታኞች እየገለጹ ነው። የምስራቅ አፍሪካ “የሰላም አባት ነኝ የሚለው ኢህአዴግ በውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ ስለሚገኝ የመወላለቅ ችግር ሳይገጠመው በፊት አሜሪካ አስቀድማ ስራዋን መስራት መጀመሯ ከራሷ ጥቅም አንጻር ነው” ሲሉ ዲፕሎማቱ እንደቀድሞው ሁሉ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። የኬሪ ጉዞም የዚሁ አካል እንደሆነ አስታውዋል። “ኢህአዴግ” አሉ ዲፕሎማቱ “የቀለም አብዮት እያለ እንደሚደነፋው ሳይሆን በመጪው ምርጫ በሩን ከፍቶ ለመወዳደር ከተስማማ ብቻ የለመደው ርጥባን ይሰጠዋል የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል።